ወቅታዊ ጉዳይ፡ ኢህአዴግ ኢህአዴግ ነው?

ድምፂ ወያነ፡ ሚያዝያ 8 ቀን 2011 መግብያ.....የመደመር ፖለቲካውን ተከትሎ ከተፈጠሩ አካራካሪ ጉዳዮች አንዱ የኢህአዴግ ህልውና ነው፡፡ የለውጡ አራማጆች ኢህአዴግ ከምንጊዜውም በላይ ጠንከራ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግ ፈርሷል ፡፡ የለም የሚሉ ወገኖችም የዛኑ ያህል ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ጉዳይ ላይ ኢህአዴጎቹ ራሳቸው በሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንደኛው ኢህአዴግ አለ ይላል፡፡ ሌላኛው ኢህአዴግ የለም ይላል፡፡ ለመሆኑ ኢህአዴግ ኢህአዴግን ሆኖ እየሰራ ነው ወይስ አሁን ያለው ኢህአዴግ ሌላ ነው?

1. ገዥ አስተሳሰብ
---------------
ቀኑን በውል ባላስታውሰውም አቶ በረከት አክሱም ሆቴል ጥንታዊ ፅሁፍ እያቀረቡ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አቶ በረከት ኢህአዴግን በሚመለከት የራሳቸውን አሳብ አቀረበዋል፡፡ በአቶ በረከት እምነት ኢህአዴግ ገዥ አስተሳሰብ ነው፡፡ ገዥ አስተሳሰቡ አለ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ አለ፡፡ ለአቶ በረከት ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ቢሆንም ባይሆንም ገዥ አስተሳሰቡ እስከአለ ድረስ ኢህአዴግ አለ፡ የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚጠፋው ገዥ አስተሳሰቡ ሲጠፋ ነው፡፡

በእርግጥ ከአቶ በረከት ጋር እኔም የምስማማው የኢህአዴግ ልማታዊ አስተሳሰብ ህዝባዊ መሰረቱን አላጣም፡፡ በአርሶ አደሩና በሰፊው ህዝብ ዘንድ የኢህአዴግ ልማታዊ አስተሳሰቦች አሁንም አሉ፡፡ ነገር ግን እዚህ አሳብ ላይ አንድ ችግር ማንሳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ገዥ አስተሳሰቡ ላይ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የለም፡፡ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ብቻ ሳይሆን አንዳንዱ ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ በምያስገርም ፍጥነት ድምጥማጡ እየጠፋ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ኢህአዴግ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የለም፡፡

2. የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት
--------------
በእርግጥ አቶ በረከት አንዳሉት የኢህአዴግ ልማታዊ አስተሳሰብ ጠፍቷል ማለት አይቻልም፡፡ መንጋውን በራሳቸው አጀንዳ በሚቦጠቡጡ ለሂቃኖችና የስልጣን ጥመኞች ታፍኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የልማታዊ አስተሳሰቡ አሁንም አልጠፋም፡፡ በመዋቅር ደረጃ ቢሆንም የልማታዊ አስተሳሰቡ አልጠቀየረም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ አምጥቻለው የሚለው የለውጥ ኃይል የለወጠው የፖለቲካ አስተሳሰብ የለም፡፡ ለምሳሌ የመደመር ፍልስፍና የሚባለው የልማታዊ አስተሳሰቡን መተካት የሚችልበት ጠንካራ የፖለቲካ መስመር የለውም፡፡ ስለዚህ አሁንም የኢህአዴግ ገዥ አስተሳሰብ ከመዋቅሩም ውስጥ ቢሆን ጠፍቷል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ከሌለ ኢህአዴግ አለ ማለት ይቻላል ወይ?

ዶር ደብረፅዮን ለደቡብ ክልል ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ በኢህአዴግ ውስጥ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት አለመኖሩን ይገልፃሉ፡፡ አንደኛው በሌላ በኩል ይሄዳል፡፡ ሌላውም በራሱ መንገድ ይሄዳል፡፡ ምን አልባት ዶር ደብረፅዮን ተሳስተው ይሆን? የአስተሳሰብ አንድነት የለም ያሉት የአሳብ ልዩነቶችን ቢሆንስ? በኢህአዴግ የአሳብ ልዩነት ማሳየት የተለመደ ሂደት ነው፡፡ የአሳብ ልዩነቶች ድርጅቱን ያጠናክሩታል አንጂ ኢህአዴግን አያፈርሱትም፡፡፡ ስለዚህ የአሳብ ልዩነት መኖሩ መዋቅሩ አለመኖሩን አያሳይም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ይሄ ጉዳይ የአስተሳሰብ ልዩነት አይመስልም፡፡ ዶር ደብረፅዮን እንዳሉት ከዚህ በፊት የነበሩ የአሳብ ልዩነቶች በአንድ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ የሚስተናገዱ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ግን የአሳብ ልዩነት ሊባል የሚችል ባህሪ የለውም፡፡ ምክንያቱም የአሳብ ልዩነት ሊያስተናግድ የሚችለው የኢህአዴግ መስመር ፈርሷል፡፡ ወይም በተፃራሪ አስተሳሰቦች ተወርሷል፡፡ ከኢህአዴግ አስተሳሰብ ጋር የሚፃረሩ አስተሳሰቦች በኢህአዴግ ውስጥ ራሳቸውን ችለው ቆመዋል፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት ያለመኖሩ መገለጫም ከኢህአዴግ አስተሳሰብ ጋር የሚፃረሩ አስተሳሰቦችን የሚከተሉ ወገኖች የፓርቲው አባል ሆነው መቀጠላቸው ነው፡፡ አባል ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉበት አቅም ፈጥረዋል፡፡ ስለዚህ አንደኛው የኢህአዴግን አስተሳሰብ ሲያራምድ ሌላው ተፃራሪ አሳብ እያራመደ ነው ማለት ነው፡፡ ከተግባርም አንፃር የድርጅቱ መዋቅራዊ አሰራር እንደበፊቱ የቀጠለ አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የአስተሳሰብ አንድነት ከሌለ የተግባር አንድነት ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚህ የድርጅቱ መዋቅራዊ አሰራር አንፃር አንዱ የሚሰራውን ሌላው እያፈረሰው የድርጅቱን መዋቅራዊ ባህሪዎችን አጥፍቶታል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ኢህአዴግ ኢህአዴግ አይደለም፡፡ እና አሁን የምናየው ኢህአዴግ ማን ነው?

4. ኢህአዴግ የሚመስል ኢህአዴግ
---------------------
በእርግጥ አሁን ላይ ኢህአዴግ የህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ የለም አንዳይባል ገዥ አስተሳሰቡ አለ፡፡ አለ እንዳይባል መዋቅራዊ ባህሪውን እያጣ ነው፡፡ ኢህአዴግ እስከአሁን ይፋ በሆነ መንገድ በምርጫ ቦርድ አልፈረሰም፡፡ ከውጪ ሲታይም መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፡፡ ከውጪ ሲታይ በእርግጥም ኢህአዴግ ያለ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሙሉ በሙሉ የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ በኩል ነው፡፡ አሁን ያለው ኢህአዴግ ኢህአዴግ የሚመስል ኢህአዴግ አንጂ ራሱ ኢህአዴግ አይደለም፡፡

አሁን ያለው ኢህአዴግ ሌላ ባህሪ ተላብሶ ጥገኛ ኢህአዴግ የሚመስል ነው፡፡ የራሱን ባህሪም ሙሉ በሙሉ አለቀቀም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ጥገኛ መዋቅር ሆኗል፡፡ ኢህአዴግ ጥገኛ መዋቅር ሆኗል ሲባል ምን ማለት ነው? ኢህአዴግ ጥገኛ መዋቅር ተበልቷል ማለት ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ ለጥገኛ አጀንዳ የሚታገለው ጥገኛ ኃይል ወርሶታል፡፡ ይሁን አንጂ ኢህአዴግ በጥገኛው ኃይል ሙሉ በሙሉ ግን አልተወረሰም፡፡ የኢህአዴግን የምትገልፅ የተወሰነች ባህሪ አለች፡፡ ጥገኛው ኃይል የበላየነት ስላገኘ አሁን ያለው ኢህአዴግ ኢህአዴግ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ኢህአዴግ ላልሆነ አላማ የሚታገል ጥገኛ ኢህአዴግ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት ዝርዝር አሳቦችን ይዤ ለመምጣት እሞክራለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን ቸር እንሰንብት!

(በመንሱር ዓሊ)